Announcement በተፈሪ መኮንን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የ“ወርቃማው ሰኞ” የልምድ ልውውጥ መድረክ በደመቀ ሁኔታ ተካሄደ ።

በተፈሪ መኮንን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የ“ወርቃማው ሰኞ” የልምድ ልውውጥ መድረክ በደመቀ ሁኔታ ተካሄደ ።

07th July, 2026

🇪🇹29/10/2018 ዓ.ም🇪🇹

የተፈሪ መኮንን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በ2018 ዓ/ም ሲያካሂዳቸው የቆያቸውን የ“ወርቃማው ሰኞ” (Golden Monday) የውይይትና የልምድ ልውውጥ መድረኮች ማጠቃለያ ፕሮግራም በዛሬው ዕለት በኮሌጁ የመሰብሰቢያ አዳራሽ በደመቀ ሁኔታ አካሂዷል።

በዕለቱ የኮሌጁ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ዲን አቶ ደመላሽ ተስፋዬ “የአመራር ልምድ (Leadership Skills)”በሚል መሪ ቃል ለኮሌጁ ማህበረሰብ ጥልቅ የሆነ ስልጠና ሰጥተዋል። ምክትል ዲኑ በገለጻቸው፤ አመራር በየደረጃው ሊኖረው የሚገባው ክህሎት ለሁሉም የኮሌጁ አካላት አስፈላጊና መሰረታዊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል። አክለውም በተቋም ውስጥ ስራዎች ስኬታማ እንዲሆኑ እርስ በርስ መተማመንና ታማኝነት፣ የቡድን ስራና ግልፅነት፣ውጤታማ የኮሙኒኬሽንና የግጭት አፈታት ስልቶች፣ስሜትን የመግዛት ፣ የመቀስቀስ እና ባለራዕይ የመሆን ክህሎቶች ያሉት አመራርና ሰራተኛ መኖሩ የተቋሙን ራዕይና ተልዕኮ ለማሳካት ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የኮሌጁ የቢዝነስ አሰልጣኝ እና የ“ወርቃማው ሰኞ” ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ነገሰ ተፋረደኝ በበኩላቸው፤ በ2018 ዓ/ም 45 የ“ወርቃማው ሰኞ” የውይይት መርሃ ግብሮች በተሳካ ሁኔታ መካሄዳቸውን ገልጸው፣ ለዚህም የኮሌጁ ማህበረሰብ ላሳየው ከፍተኛ ቁርጠኝነት ምስጋና አቅርበዋል። ኮሌጁ እየተገበረው ካለው የISO 21001:2018 EOMS መስፈርት ጋር በማጣመር የእውቀት ሽግግርን በስፋት መስራት መቻሉን አስረድተዋል። በተጨማሪም አቶ ነገሰ “ሶስት አይነት ሰው፣ ሶስት አይነት ድርጅት” በሚል ርዕስ አሳታፊ ውይይት በመምራት፣ የኮሌጁ ማህበረሰብ አባላት ራሳቸውንና ድርጅታቸውን እንዲገመግሙ መነሻ ሃሳብ አቅርበዋል።

የፕሮግራሙን ማጠቃለያ ንግግር ያደረጉት የኮሌጁ ዲን አቶ ተሾመ ፈይሳ እንደገለፁት ይህ የ“ወርቃማው ሰኞ” የውይይት መድረክ በ2018 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ በክብርት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አበቤ አማካኝነት በጽህፈት ቤታቸው መጀመሩን አስታውሰዋል። መርሃ ግብሩ በከተማ አስተዳደሩ ተቋማት ውስጥ የነበረውን “ብላክ መንደይ” (አሰልቺ/ደባሪ ሰኞ) የሚለውን አስተሳሰብና የስራ ስንፍና በ“ወርቃማው ሰኞ” ንቁና ውጤታማ የስራ መንፈስ ለመቀየር የተጀመረ ትልቅ ንቅናቄ መሆኑን ገልጸዋል።

ዲኑ አክለውም “እንደ ተቋም ይህ መርሃ ግብር የእውቀት አስተዳደር ስርዓት (Knowledge Management) መገንቢያ መሳሪያችን ነው፤ እያስተዳደርን ያለነው እውቀትን በመሆኑ ኮሌጃችን ትልቅ ስራ ሰርቷል” በማለት መርሃ ግብሩን በበላይነት ሲያስተባብሩና ሲመሩ የነበሩትን የቡድን አባላት በላቀ ምስጋና አበረታተዋል።

.

Copyright © All rights reserved.

Created with